የዕድራችን ዓመታዊ ጠቅላላ ስብሰባ ቅዳሜ መጋቢት 26/2018 ዓ.ም ስለሚደረግ በዕለቱ እንድትኙልን በትህትና እንጠይቃለን፡፡
ማሳሰቢያ፡ በማይገኙ አባላት ላይ በመተዳደሪያ ደንብ መሰረት $150 ቅጣት ተግባራዊ ይሆናል፡፡
ሰዓት 1፡00 PM
Date: April 4, 2026
ዕድር የሚለው ቃል ብዙ አይነት ፍቺ አለው ይኅውም ፣ ዘየ ወይም ልማድ ይሆናል፣ ለምሳሌ የእገሌ ሀገር ዕድር እንዲህ ነው ሲል ልማዱ ዘየው እንዲህ ነው ማለት ይሆናል ። ኅብረት፣ አንድንት ማለት ይሆናል ፣ይህንም የመሳስሉ ልዩ ልዩ ትርጉሞች አሉት ግን አሁን በዚህ ዘመን የሚታየው የስራው አፈፃፀም የሚያመለክተው ሁለተኛውን ቁጥር የመሰለ ሆኖ እናገኘዋለን። ስለዚህ ዕድር ማለት አሁን ለቀብር ጊዜ የሚያገለግል ዉል ፣የቀብሩን ስረዓት የሚመለክት ገንዘብ የሚዋጣበት አገልግሎት ነው። ይህም ማለት አንድ ሰው ኃዘን ሳይደርስበት አስቀድሞ ገንዘብ ያዋጣል የተለያየ ሃሳብም ይለዋወጣል ፣ እንደዚሁ አድርገው የሚያዋጡት ገንዘብ ይህም የሚወስኑት ውሳኔ ማህበሩም በጠቅላላ የሥራውም አፈፃፀም ነው ። ዕድር መልኩን ለውጦ ነው እንጂ እዝን ከምንለው ጋር በጣም ይመሳስላል እንዲያዉም እርሱን አሻሽሉት መልኩን ለወጡት ለማለት ይቻላል ፣ ምክንያቱም እዝን በዚያው በአደጋው ዕለት የሚያዋጡት ወይም የሚሰጡት ነገር ሲሆን ዕድር ግን አስቀድሞ የተወሰነ ገንዘብ ሲያዋጡ ቆይተው ቦሀላ በሀዘኑ ፣ በችግሩ ጊዜ የሚረዱት ወይም እርዳታ የሚሰጡበት አገልግሎት ነው ።
ምንጭ : ማህበራዊ ኑሮ በኢትዮጵያ( በሊቀ ስልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ)
ክፉ ሀዘን የወለደው ተቋም፥ የቅዱስ ያሬድ መረዳጃ ዕድር እንዴት ተመሰረተ? በመስከረም 2016 ዓ.ም የበዓል ደፋ ቀና በሚባልበት ወቅት፣ አየሩ ደስ የሚልና የሚያምር ሆኖ ሳለ፣ በኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ኆኅተ ምሥራቅ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አዳራሽ ውስጥ ለአንድ ወንድማችን ሀዘን ተቀምጠን ነበር። ሀዘንተኛውና ቤተሰቡ ከፊታችን ተቀምጠው ሳሉ፣ በአንጻሩ የነበሩ ወንድሞችና እህቶች ሀዘንተኛውን በገንዘብ እንዴት እንርዳ?” በሚል ጉዳይ አንዴ ወደ ውጭ፣ አንዴ ወደ ኩሽና፣ እንዲሁም ወደ አዳራሹ ተመላልሰው በሀዘን የተሞላ ነገር ግን የሞቀ ውይይት ያደርጉ ነበር። ሀዘንተኛውና ቤተሰቡ ከከባድ ሀዘናቸው በተጨማሪ በገንዘብ ጉዳይ መጨነቃቸው ሌላ ጭንቀት ሆኖባቸው ነበር። ይህ ሁኔታ በማኅበረሰባችን ውስጥ ተለመዶ የሚታይ አሳዛኝ ኑሮ ነው፤ አስክሬን ፊት ቁምን ጃንጥላ ዘርግተን ገንዘብ መሰብሰብ፣ ወይም ሀዘንተኞችን አንገታቸውን በሚያስደፋ መልኩ ስማቸውንና የጓዳቸውን ጉዳይ እያነሱ በGoFundMe ገንዘብ መሰብሰብ የተለመደ ነው። ይህ አሳዛኝ፣ እውነታ ነው የቅዱስ ያሬድ መረዳጃ ዕድርን እንዲወለድ ያደረገው።
ስለ ዕድር መመስረት ውይይት ቀደም ሲል በብዙ ጊዜያት ተነስቶ ነበር፤ነገር ግን በመስከረም 2016 ዓ.ም የተፈጠረው ይህ ክስተት እና ያንን ተከትሎ የተደረገው ውይይት ለተግባር የሚያደርስ ፍሬ አፈራ። ውይይቱ ለመጀመር መጀመሪያ የደወልሁት ለአቶ ይርጋለም ነበር። ሀሳቡ በጣም ደስ አለው፤ ወዲያውኑም የተለያዩ ዕድሮችን ተሞክሮ መሰብሰብ ጀመረ። እኛም ሁለታችን ተከታታይና ቋሚ ውይይት አደረግን። እርሱ ከተለያዩ ሰዎች ጋር በመወያየት ሀሳቦችን ሰበሰበ፣ የዕድር መመስረት ሀሳቡም ተግባራዊ ቅርጽ እንዲይዝ አደረገ። በወርኃ ጥቅምት 2016 ዓ.ም፣ ከመልአከ አርያም ብርሃኑ ጎበና እና ከሊቀ ካህናት አብርሃም ጋር፣ ከእሁድ አገልግሎት በኋላ በሰንበቴ ቤት ተቀምጠን ስለ ዕድሩ ምሥረታ በዝርዝር ተወያየን። በዚህ ውይይት የዕድሩ መሠረታዊ ምሰሶዎች ተቀመጡ፤ ለምሳሌ የዕድሩ አባል ለመሆን የደብሩ ሰበካ ጉባኤ አባል መሆን ግዴታ መሆኑ፣ እንዲሁም በዕድሩና በሰበካ ጉባኤ መካከል ሊኖር የሚገባው ግንኙነት በግልጽ ተወሰነ። በተጨማሪ የዕድሩ መስራች የኮሚቴ አባላትም የተለዩት በዚች ቀን በዕለተ ሰነበት ነበር። በጥር ወር 2017 ዓም ሰበካ ጉባዔ ተወያይቶ ዕድሩ አንዲመሰረት ውሳኔ አሳለፈ። በዕድሩና በደብሩ መካከል መኖር ስለሚገባው ግንኙነት በዝርዝር ወሰነ። ይህ የሰበካ ጉባኤው ዝርዝር ውሳኔ በኋላ በዕድሩ መተዳደርያ ደንብ በተለያየ አንቀጽ ተካቷል። የዕድሩ መስራች የኮሚቴ አባላት የሚከተሉት ነበሩ፤ ሊቀ ካህናት አብርሃም፣ ወ/ሮ ማህሌት፣አቶ ብዙአየሁ፣አቶ ቴዎድሮስ፣አቶ ቦጋለና አቶ ግዛቸው ናቸው። ይህ መስራች ኮሚቴ በጸሎት፣በፍቅር በፍጹም መግባባት እና በትጋት በማገልገሉ ነበር ያንን በጣም አስቸጋሪ የምስረታ ሂደት ማለፍ የተቻለው። አግዚአብሔር አምላክ ዕድሩ ወገን የሚጠቅም አንዲሆን የአገልጋዮቹን አገልግሎት እንዲቀበል እንዲሁም አባሉትንና ቤተሰባቸውን በረድኤት እንዲጠብቅ በጸሎት አባቶች አንዲለምኑ የዕድሩ መስራች የኮሚቴ አባላት ጸሎተ መባ ኢትዮጵያ ለሚገኙ ገዳማት ይልኩ ነበር።
እንዲህ ተደርጎ መስራች ኮሚቴው የቅዱስ ያሬድ መረዳጃ ዕድር የምስረታ ጉባኤውን ሚያዝያ 12 የቅዱስ ሚካኤል ዕለት 2016 ዓ ዓ.ም አዘጋጀ። ዕድሩ ተወለደ። የመጀመርያ የዕድሩ ሥራ አስፈጽሚና የኦዲትና ቁጥጥር አባላትም ተመረጡ። ዕድሩ በይፋ በጠቅላላ ጉባኤ ከተመሰረተ በኋላ ከነበሩ መሰረታዊ ሥራዎች አንዱ የሒሳብ አሰራርን መዘርጋት ነበር። የሥራ አስፈጽሚ አባልና የሒሳብ ክፍል ተጠሪ አቶ ኒቆድሞስ የሒሳብ አሰራሩን በጥሩ ሙያዊ አሰራር በደንብ አድርገው ዘርግተውታል። አሁን ለአለው ወጥ ግልጽና ሙያዊ የዕድሩ የሒሳብ አሰራር አቶ ኒቆድሞስ ባለውለታ ናቸው። የቅዱስ ያሬድ መረዳጃ ዕድር የተመሰረተው ዓላማው ተልዕኮውና ርዕዩም የተቀረጸው ሦስት ተቋማትን መሰረት አድርጎ ነው። የመጀመርያው የዳበረውንና ውብ ባህላዊ ትውፊት የሆነውንና የሀዘን ጊዜ የሚደረገውን የመረዳዳት ኢትዮጵያዊ ባህላዊ ተቋም የሆነውን ዕድር ነው። ሁለተኛ የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን የማህበራዊ ወንጌል ተልዕኮ ነው። ስለሆነም የዕድሩ ተልዕኮ የወንጌል አገልግሎት ነው። ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፥ ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ ሮሜ 12፤15) እንደሚል። ዕድሩን የሚመሩና ለዕድሩ የሚሰሩ ሁሉ የወንጌል አገልጋዮች ናቸው። ተግባሩም የጽድቅ ሥራ ነው። የአባላቱ ማኅበራዊ መሰረትም ቤተክርስትያን ናት። ስለሆነም ነው ሁሉም የዕድሩ አባላት በአሜሪካን ሀገር በሜሪላንድ ግዛት የምትገኘው የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ኆኅተ ምሥራቅ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ አባላት ናቸው። የዕድሩ መተዳደርያ ደንብም ሆነ መመርያው የተቀረጸው ይህን የማኅበራዊ ወንጌል አገልግሎት መሰረት አድርጎ ነው። ይህ የዕድሩን ተልዕኮ ግልጽ አድርጎታል። አሰራሩን አቅሎ የዕድሩ አመራሮች ጽድቅን እያሰቡ የሚለፉ አገልጋዮች አድርጎአቸዋል። ሦስተኛ የመድን (ኢንሹራንስ) አሰራርን መሰረት በማድረግ ነው። የቅዱስ ያሬድ መረዳጃ ዕድር ዘመኑን የዋጀ እንዲሆንና በሀዘን ወቅት ከሚደረገው መተጋገዝ በተጨማሪ አባላት በኢኮኖሚው ችግርም ወቅት የሚረዳዱበት አንዲሆን የመድን (ኢንሹራንስ) ቅርጽ አንዲኖረው ታስቦ የተቋቋመ ነው። ይህ በሁለት አይነት ይገለጻል አንደኛው ዕድሩ አንደተቋም ኢንቨስት አድርጎ ተቋማዊ የሀብት አቅሙን ማሳደግ ሲሆን ሁለተኛ አባላት አንደ አቅማቸው ተጨማሪ ገንዘብ አውጥተ በጋር ኢንቨስት የሚያዳርጉበት ነው።